የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ያጋጠሙ አደጋዎችና ተግዳሮቶችን ለመፍታት አይተኬ ሚና ተጫውተዋል ተባለ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ውጤታማነት እንዲሆን አይተኬ ሚና መጫወታቸው ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አዘጋጅነት ሰብአዊነትና የሚዲያ ተቋማት ሚና በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ውጤታማ እንዲሆን አይተኬ ሚና መጫወታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክትር ሊያ ታደሰ ገልፀዋል::
የሰብአዊነት፣ የአብሮነትና የመቻቻል እሳቤ በሕዝቦች ዘንድ እንዲሰርፅ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት አስተዋፅኦ ከፍ ያለ መሆኑን በመገንዘብ መስራት ይገባልም ተብሏል፡፡
የጤና ሚኒስቴርም እንደ ሀገር ያጋጠሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ጫናዎችን በመቀነስ ረገድ እየሰራ ያለውን የሰብአዊ ድጋፎችና ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል::
ባለፉት ጊዜያት በጦርነት አማካይነት ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ተጎጂ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በርካታ መሆናቸውን ያነሱት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሆኖም እነዚህ አካላት የሰብአዊ እርዳታን እንዲያገኙ የለጋሽነት ስሜትን በሕዝቦች ዘንድ በማስረፅ ለተጎጂዎችና ተፈናቃዮች ለመድረስ የተጀመረው የሃብት ማሰባሰብ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ገልፀዋል
::
መገናኛ ብዙኃን የአራተኛው መንግሥት ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ የኢትዮጵያውያን እሴት የሆነውን የመተጋገዝ እና የመተባበር እሴት እንዲያብብ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ተብሏል::
በምክክር መድረኩም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል::
በሔብሮን ዋልታው