መንግሥት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይ እርምጃ እወስዳለው አለ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) መንግሥት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይነት ያለው እርምጃ አንደሚወስድ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
መንግስት በሰጠው አቅጣጫና የሀገሪቱ ብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን በወሰነው መሰረት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻልና ገበያውን ለማረጋጋ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ እንዲገባ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለኅብረተሰቡ እየተከፋፋለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ደግሞ በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ ተጠቃሎ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ድፍድፍ ዘይት ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ሦስት ፋብሪካዎችም ምርቶቻቸውን ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የውጭ ምንዛሬ ተመቻችቶላቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ የምግብ ዘይት እጥረትን ለዘለቄታው ለመፍታትም እንዲቻልም ለሌሎች አቅራቢዎችም ዘይት ከውጭ አስመጥተው ለመንግሥት እንዲሸጡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የኑሮ ወድነትን ለመቅረፍ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት የምግብ ዘይት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ በማድረጉ 23 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ያጣ ሲሆን ለነዳጅ የ100 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡