ለኦነግ ሸኔ የሎጂስቲክ ሥራ ሲያከናውን የነበረ ግለሰብ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) ናኒ ቤኛ የተባለ ግለሰብ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ጎሮ ሰፈራ የግለሰብ ቤት ተከራይቶ ለአሸባሪው ኦነግ ሸኔ የሎጂስቲክ ሥራ ሲያከናውን እጅ ከፍንጅ ተያዘ፡፡

በከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ በመከላከያ መረጃና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በተሰራ ሥራ ከናኒ ቤኛ በተጨማሪ ሌሎች 7 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለሽብር አላማ ሊያውሉዋቸው የነበሩ የቀድሞ መከላከያ የደንብ ልብስ፣ በርካታ ቁጥር ያለው የተለያዩ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች፣ የተለያዩ የባንክ ኤቲኤም እና የተለያዩ ሰነዶች በተከራዩበት ቤት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የአከራይ እና ተከራይ ውል ሳይኖራቸው በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ 8 ሆነው ሲኖሩ እንደነበረ ተገልጿል፡፡
አከራዮች ቤታቸውን ሲያከራዩ የተከራዮች ማንነት የሚገልጽ መረጃ ጠይቀው ማከራየት እንደሚገባቸው የጸጥታ ግብረ ኃይሉ ማሳሰቡን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ኅብረተሰቡ ጸጉረ ልውጦችን ሲያገኙ በአቅራቢያቸው ላሉ የጸጥታ ኃይሎቸች ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡