የታሪክ ምሁር ስንታየሁ ቶላ የቀብር ሥነ ሥርዓት በሰበታ ከተማ ተፈጸመ

የስንታየሁ ቶላ የቀብር ሥነ ሥርዓት

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የኦሮሞ ባህልና ታሪክ ምሁር ስንታየሁ ቶላ የቀብር ሥነ ሥርዓት በሰበታ ከተማ ተፈጸመ።

ስንታየሁ ቶላ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከባለሙያነት እስከ ምክትል ቢሮ ኃላፊነት በሀገር ደረጃ ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የኦሮሞን ሕዝብ ያስተዋወቀ በርካታ ሥራዎችን የሰሩ ታላቅ ምሁር ነበሩ።

ያደረባቸው ድንገተኛ ህመም እስኪያጋጥማቸውና ለህልፈት እስኪዳረጉ ድረስም የኦሮሞ ጥናትና ምርምር እኒስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

የታሪክ ምሁሩ ስንታየሁ ቶላ ለኦሮሞ ሕዝብ ብሎም ለሀገሪቱ ከፈፀሟቸው ተግባራት መካከል የገዳ ሥርዓት ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ሀብቶች መካከል እንዲሰፍርና በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የአንበሳውን ድርሻ የተወጡ ሰው መሆናቸውም ተጠቁሟል።

የኦሮሞ ሕዝብ በአድዋ ድል፣ በሳምቤና በሌሎች የድል አውድማዎች ያበረከተውን ሚና በጥናት በማሳየት የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያዊያን ጋሻ መሆናቸውን ማሳየት መቻላቸውም ተመላክቷል።

ከገዳ ሥርዓት በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ቅርሶች የሶፍ-ዑመር ዋሻ፣ ድሬ ሼክ ሁሴን፣ የባሌ ተራሮች ፓርክና ሌሎችም በየኔስኮ ለመመዝገብ በእጩነት እንዲቀርቡ ጠንካራ ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል።

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የመንግሥት ባለ ስልጣናትም በተገኙበት ተፈጽሟል።

የታሪክና የኦሮሞ ባህል ምሁሩ ስንታየሁ ቶላ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።

ቡላ ነዲ (ከሰበታ)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW