ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአቅመ ደካማ ቤቶችን አፍርሶ የመገንባት ሥራ አስጀመሩ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ጨርቆስ አካባቢ እጅግ የተጎሳቆሉ ሁኔታ ያላቸውን አርባ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ መልሶ በአዲስ መልኩ የመገንባት ሂደት አስጀምረዋል፡፡

ከንቲባዋ ሄይኒከን ቢራ ፋብሪካ በበጎ ፍቃድ በትብብር በሚያስገነባው በዚህ ግንባታ ማስጀመሪያ ላይ ከተማን ማልማት የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በሚወጡ ተቋማትና ባለሃብቶች ጭምር እንጂ ብለዋል፡፡

ሌሎችም ከመንግሥት ጋር በጋራ ለከተማዋ ዕድገትና ለነዋሪዎቿ ብልጽግና ማኅበራዊ ኃላፊነቱንን ለመወጣት እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል።

የሄኒከን ቢራ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሁበርት ኢዝ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩትን ነዋሪዎች ህይወት ለማሻሻል መስራት የኛም ኃላፊነት ነው፤ በመሆኑም በአጭር ጊዜ አጠናቀን ለተጠቃሚው እናስረክባለን፤ ለዚህም ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዘመኑ ደሳለኝም በበኩላቸው ቤቶቹን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ለነዋሪው እናስረክባለን በማለት ቃል መግባታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW