ለደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እየተሰጠ ነው

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) ለደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች “አዲስ ፖለቲካዊ እይታ፤ አዲስ ሀገራዊ እምርታ” በሚል መሪ ሀሳብ በ 4 ማዕከላት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ጥላሁን ከበደ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት በየደረጃው ያለው የፓርቲው አመራር ሀገራችን የገጠማትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት እንዲችል የአመራሩን ብቃት ማጎልበት ይገባል።

የፓርቲው ዓላማ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ ነው ያሉት ኃላፊው ይህንንም ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ውስብስብና መገመት የማንችለው ነው ያሉት አቶ ጥላሁን ይህንን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እና የህዝባችንን ጥያቄ በብቃት መመለስ የሚቻለው አመራሩ ቁርጠኛ መሆን ሲችል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በፓርቲው ጉባኤ ታሪካዊ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እንደተቻለ የተናገሩት ኃላፊው በተለይ በምርጫ ወቅት ለህዝቡ ቃል የገባናቸውን ጉዳዮች በተግባር ለማሳየት በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉም ጠቁመዋል።

በስልጠናው የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።