ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ በቀድሞው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ኅልፈት የተሰማቸውን ኀዘን ገለጹ

ግንቦት 12/2014 (ዋልታ) ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በቀድሞው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ ኻሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ኅልፈት የተሰማቸውን ኀዘን አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ተገኝተው ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ በኤምባሲው በቸዘጋጀው የኀዘን መግለጫ መዝገብ ላይ “በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሼክ ኻሊፋ ቢን ዛይድ አል ናሀያን ኅልፈት የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን በራሴ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ለመግለጽ እወዳለሁ” የሚል መልዕክት አስፍረዋል።

ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሕዝብ እና መንግሥት፣ ለአዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ለንጉሳውያን ቤተሰቡም መፅናናትን ተመኝተዋል ሲል ኢብኮ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ በኀዘን መግለጫቸው ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትንን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስፍረዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ የተባበሩት ዓረብ ኢማሬቶችን የመሩት ሼክ ኻሊፋ ቢን ዛይድ አል ናሀያን በ73 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።

እርሳቸውን ተክተው ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሀያን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።