ኢንዱስትሪያል ፓርኩ ለሰራተኞቹ የመኖሪያ ህንፃዎችን አስገነባ

ግንቦት 12/2014 (ዋልታ) የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለ2 ሺሕ 700 ሰራተኞቹ ለመኖሪያነት ያስገነባቸውን ህንፃዎች አስመርቋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ሰለሞን ሰራተኞች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተረጋግተው እንዳይሰሩ የቤት ችግር ዋነኛው እንቅፋት መሆኑ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸው ይሄም ሰራተኞች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በፓርኮቹ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎችና ሌሎች ባለሃብቶች ለሰራተኞች ቤት ገንብተው እንዲያቀርቡ እያግባባን ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ ፓርኮቹ የሚገኙባቸው ከተሞችም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በዚህም ኢንዱስትሪያል ፓርኩ ቪንትስ የተባለ የኮርያ ኩባንያ ለሰራተኞቹ ያስገነባውን የመኖሪያ ቤት በይፋ አስመርቋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ፓርኩ የመኖርያ ቤት ባለመመቻቸቱ ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ መቆየታቸውን የሚናገሩት የኢንዱስትሪያል ፓርኩ ሰራተኞች አሁን ግን ባገኙት የመኖሪያ ቤት ከችግራቸው መላቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡

በታምራት ደለሊ