ቢሮው ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት 1 ሺሕ መጻሕፍት አስረከበ

አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት

ግንቦት 12/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በየክፍለ ከተማ ከሚገኙ ወጣቶች ያሰባሰበውን 1 ሺሕ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አስረክቧል።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆየውን የመጻሕፍት ማሰባሰብ ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንን ተከትሎ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጥበቡ በቀለ የተሰበሰበውን መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የበላይ ተጠሪ ውባየሁ ማሞ አስረክበዋል።

እንደኢዜአ ዘገባ ቢሮው ያስረከባቸው መጻሕፍት የተለያየ ይዘት ያላቸውና ትውልድን የሚቀርጹ መሆናቸው ተገልጿል።

የቤተ-መጻሕፍቱ የበላይ ተጠሪ ውባየሁ ማሞ በተማረ ኃይል የተገነባች ሀገር ለመፍጠር አንባቢ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው ይህንንም ግብ እውን ለማድረግ ለሚሰራው አብርሆት መጻሕፍት መለገስ ይገባል ብለዋል።

እውቀትን መሰረት ያደረገ ትውልድ በመገንባት የተሻለ ሀገር ተረካቢ ኃይል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሁለገቡ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከታኅሣሥ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የመጻሕፍት የማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቤተ-መጻሕፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍት የመያዝ አቅም እንዳለውም ተመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW