አዲስ ተሿሚ የመንግሥት ተጠሪዎች ሕዝባዊ አደራን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነን አሉ

ግንቦት 12/2014 (ዋልታ) በይፋ ሥራቸውን የጀመሩት አዲስ ተሿሚዎቹ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች ሕዝብ እና መንግሥት በዕምነት የጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገለጹ፡፡

በመንግሥት ተጠሪ ሚኒስቴር የስልጠና እና ዓቅም ግንባታ ዘርፍ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የተሾሙት ምሕረቱ ሻንቆ እና የሕዝብ ውክልና እና የአደረጃጀት ሥራዎች የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የተሾሙት መሠረት ኃይሌ መንግሥትን እና ሕዝብን በድልድይነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሕዝብ እንዲመለሱለት የሚሻቸው በርካታ ጥያቄዎች መመለስ እንዳለባቸው በመገንዘብ የሚጠበቅባቸው የሥራ ድርሻ እና ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚረዱ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ፓርላማው የሚያወጣቸው እና የሚያጸድቃቸው ሕጎች በአስፈጻሚው በኩል በትክክል መሬት ወርደው በሥራ መተርጎማቸውን እንደሚከታተሉም አስታውቀዋል፡፡