ሁለቱ ጄነራል መኮንኖች ለተቋማዊ ለውጡ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ግንቦት 14/2014 (ዋልታ) “በአምባሳደርነት የተሾሙት ሁለቱ ጄነራል መኮንኖች ለተቋማዊ ለውጡ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው” ሲሉ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

ለአምሳደር ጀኔራል ባጫ ደበሌ እና ለአምባሳደር ጀኔራል ሀሰን ኢብራሂም የምስጋናና የሽኝት ስነ ስርዓት በምድር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ ግቢ ውስጥ ተካሂዷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሁለቱ አምባሳደር ጄነራሎች ከለውጥ በፊትና ከለውጥ በኋላ የነበራቸው አገራዊ አበርክቶ አይተኬ እንደነበር አስታውሰው እንደተቋምም እንደሃገርም በነበሩ ውጣ ውረዶችም በጋራ በመስራት ስኬታማ ቆይታ እንደነበራቸው ተናግረዋል።

መንግስት ባለው ሃላፊነት መሰረት ሁለቱን ጄነራል መኮንኖች በአምበሳደርነት መመደቡ ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቀጣይም ከአምባሳደር ጄነራሎቹ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን በመግለፅ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡

አምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ ተቋሙ ከዚህ በፊት የመደበኛና ፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ ስራን በትክክል መስራት ባለመቻሉ በሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ተግባር ሊፈፀምበት እንደቻለ አስታውሰው በቀጣይም እንደተቋም በመደበኛና ፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንባት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ አገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር ከብሄርና ከፖለቲካ አስተሳሰብ ወገናዊነት የፀዳ ሰራዊት መገንባት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የገለፁት አምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ ይህንን ለማሳካትም በየደረጃው ያለው አመራር የራሱን ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል።

አምባሳደር ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም በበኩላቸው ከለውጥ በፊት የተሳካ የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ሂደቱ ላይ እምብዛም ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ አስታውሰው በለውጥ ማግስት በውጣ ውረድ ውስጥ በመሆን የተሰሩ ስራዎች ግን ስኬታማ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በተቋሙ ረጅም እድሜ እንደማሳለፋችን መጠን ተቋሙ በሚፈልገው መልኩ በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ነን ያሉት አምባሳደር ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም ለተደረገው የምስጋናና የሽኝት ፕሮግራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዕለቱ ሁለቱ አምባሳደር ጄነራሎች የተዘጋጀላቸውን ስጦታ ከመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ዕጅ መቀበላቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል።