ለሰላም መጠናከር የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል – የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች

የድሬዳዋ ከተማ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) በሀገሪቱ ሰላም እንዲጠናከር የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ፖለቲከኞች ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ሕዝቡን በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል የፀጥታ ችግር እንዲከሰት የሚጥሩ አካላትን ከመከላከል አንፃር ኅብረተሰቡ እርስ በእርሱ ያለውን አንድነትና ፍቅር ማጎልበትና የሃሰት መረጃዎችን ማጋለጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ድሬዳዋ የተለያዩ እምነቶች እና በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደውና ተዋልደው በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗንም በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡

ሆኖም አልፎ አልፎ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት ሕዝቡን በብሔርና በሃይማኖት ሽፋን የሰላም መደፍረስ እንዲፈጠር የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የአስተዳደሩም ሆነ የሀገሪቱ ሰላም እንዲጎለብት በተለይም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ፖለቲከኞች ሕዝቡን ስለሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት በመስበክ ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ኽዝቡ እርስ በእርሽ ያለውን አንድነትና ፍቅር በማጎልበት በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር የሚያሴሩ አካላት ምኞትን ማምከን እንደሚገባ ጠቁመው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችን መከላከልና ማጋለጥም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የሀገሪቱን ሰላም ማጠናከርና የሕዝቦችን በፍቅር አብሮ የመኖር እሴት ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተስፋዬ ኃይሉ (ከድሬዳዋ)