2ኛው የአርሶ አደሮች ፌስቲቫል በበቆጂ ተካሄደ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) ሁለተኛው የአርሲ አርሶ አደሮች ፌስቲቫል በአርሲ ዞን በቆጂ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡

ዝግጅቱን የታደሙት የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሙሳ ፉሮ አርሶ አደሩ ለመኸር እርሻ ዝግጅት እያደረግ ባለበት ወቅት ፌስቲቫሉ መካሄዱ የበለጠ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የአሪሲ አርሶ አደር የግብርና ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች ግንባር ቀደም እንደሆነ የጠቀሱት አስተዳዳሪው እንደዚህ አይነት ፌስቲቫሎች ምርታማነትን የሚያሳድግ ልምድ ያስገኛል ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አበራ ለማ በበኩላቸው በፌስቲቫሉ መካሄድ አርሶ አደሩ እርስ በእርስ ተቀራርቦ ለመስራት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልፀው ምርትን ከሚያቀነባብሩ እና ለገበያ ከሚያቀርቡ ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ ከቀረቡት የግብርና ቴክኖሎጂዎች ባሻገር የአርሲ ሕዝብ ባህላዊ ምግብ የሆነው እና 100 ኪሎ ግራም የገብስ ዱቄት የፈጀው ገንፎ ለሕዝብ ቀርቧል፡፡

አንተነህ ደጀኔ (ከበቆጂ)