14ኛው የዓለም በይነ-ዕምነት ጉባኤ በዶሃ መካሄድ ጀመረ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) 14ኛው የዓለም በይነ-ዕምነት ጉባኤ “የጥላቻ ንግግር በሃይማኖታዊና በቅዱሳት መጻሕፍት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በኳታር ዶሃ መካሄድ ጀመረ።

ከመላው አለም የተውጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና የሀይማኖት መሪዎች በተገኙበት በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አሊይ ተገኝተዋል።

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት፤ በጉባኤው ላይ ምሁራን ከተለያዩ ሀገራት ልምድ በመውሰድ ጥናት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው በነገው ዕለትም የሚቀጥል ሲሆን በማጠናቀቂያው መርሐግብር በጥላቻ ንግግር ዙሪያ ላይ በዓለም የሃይማኖት ተቋማት በሀይማኖቶች ዙሪያ የጋራ መግባባት እና አቋም ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።