የበድር ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) “እስላማዊ እሴቶች ለሀገር ሰላም እና እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የበድር ጉባኤ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው።

ከ22 አመታት በፊት አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው አለም አቀፍ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ማህበር 22ተኛውን ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

በድር ወደ ማንነት (BADR back to the root) በሚል የተዘጋጀው መርሀ ግብር በአውሮፓ እና አሜሪካ የተወለዱ ኢትዮጵያዊያን ስለ ሀገራቸው የሚረዱበት እና ኢትዮጵያን የሚያውቁበት መሆኑ ተጠቅሷል።

5 ሺሕ የሚደርሱ አባላትን ያቀፈው በድር ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዳለውም ተጠቅሷል።

በዚህም ማዕድ የማጋራት እና በልማት ማህበራት ውስጥ የሚሳተፍ ሲሆን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጎ ፈንድ ሚ በመክፈት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ 1 ሚሊዮን 50 ሺሕ ዶላር ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

22ተኛው ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱ በኮሮና ወረርሽኝ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ከማነቃቃት ባለፈ የውጭ ምንዛሬን እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።

በመርሀ ግብር ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡ እና ማንነትን የማሳወቂያ መድረክ እንደሚዘጋጅ የተጠቀሰ ሲሆን የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችም ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡

እስካሁን ከ1 ሺሕ 500 በላይ የሚሆኑ ታዳሚያን የተመዘገቡበት የበድር ጉባኤ ከሐምሌ 8 እስከ 18 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድም ተገልጿል።

በሃኒ አበበ