ኮርፖሬሽኑ የቱርክ ባለሃብቶች በአዳዲስ መስኮች እንዲሰማሩ ምቹ ምህዳር እፈጥራለው አለ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን የቱርክ ባለሃብቶች በአዳዲስ መስኮች እንዲሰማሩ ምቹ ምህዳር እንደሚፈጥር አስታወቀ፡፡
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይታቸው በዋናነት የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚሰማሩባቸውን የኢንቨስትመንት መስኮች መለየት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ አሁን እየሠራቸው ስላሉ ተግባራት ለአምባሳደሩ ገለፃ መደረጉን የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የቱርክ ባለሃብቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በአጋርነት ሊሰማሩባቸው የሚችሉ የኢንቨስትመንት መስኮችን ለመለየት መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ቱርክ የኢንቨስትመንት ትስስራቸውን የሚጠናክሩበት ሁኔታዎችን ለመፍጠርና በቅርበት ለመስራት በውይይቱ ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የቱርክ ባለሃብቶች በአዳዲስ መስኮች እንዲሰማሩ ኮርፖሬሽኑ ምቹ ምህዳር እንደሚፈጥርም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያረጋገጡት፡፡