ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በሚቀጥለው ወር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊመክሩ ነው

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመምከር በሚቀጥለው ወር በአዲስ አበባ የሚኒስቴሮች የጋራ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት  በናይጄሪያ ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተከትሎ ነው መርኃ ግብሩን ለማከናወን ከስምምነት የተደረሰው፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን ሥራ እና በሌሎችም ዓለም ዓቀፍ የሁለትዮሽ  ጉዳዮችን ለማጠናከር መስማማታቸውን የናይጄሪያ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡

ስለሁለቱ ሀገራት ግኑኝነት አስተያየት የሰጡት በኢትዮጵያ የናይጄሪያ አምባሳደር ቪክቶር አዴሌክ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ወደፊትም ቢሆን በሀገራቱ የጋራ ጥቅም ላይ በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒትሩ የናይጄሪያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ማላቦ በሚደረገው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ስብሰባው በአፍሪካ አህጉር እያቆጠቆጠ በመጣው ሽብርተኝነት፣ ኢ-ሕገመንግሥታዊ የስረዓት ለውጥ እና ሰብአዊ ድጋፍ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡