በኢትዮጵያ በየዓመቱ 3 ሚሊየን ሰዎች ይወለዳሉ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ 3 ሚሊየን ሰዎች እንደሚወለዱ ተገለጸ፡፡

አንድ ቤተሰብ በአማካይ 3 ልጅ የሚኖረው ሲሆን በክልሎች ደግሞ ይህ ቁጥር ከፍ ይላል።

ለአብነትም በሶማሌ አንድ ቤተሰብ ያለው የልጅ ብዛት በአማካይ ሰባት እንደሆነ ነው የተገለፀው።

ይህም በከፍተኛ መጠን የህዝብ ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶችን እያስከተለ ይገኛል።

የጤና ሚኒስቴርም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን እየተገበረ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ እና ከ22 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት አካል የሆነው ብሔራዊ የፕሮጀክት ትግበራ ላይ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማዕከል በ12 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እየተገበረ ከሚገኘው ጥቅል ፕሮጀክት አንዱ ክፍል የሆነው የተመጠነ፣ ደስተኛ እና ውጤታማ የሆነ ቤተሰብ ፕሮጀክት 2ኛ ክፍል ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2024 ይተገበራል ተብሏል።

የፕሮጀክቱ ዓላማ የስነ ተዋልዶ ጤና እና የፆታ እኩልነትን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረግና የእናቶች ሞት ምጣኔ እንዲሁም ያልተመጠነ ቤተሰብ እንዲቀንስ ማስቻል ነው።

ፕሮጀክቱ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች ይተገበራልም ተብሏል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ በአውደ ጥናቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ በቤተሰብ ምጣኔ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እንዲሁም የተመጠነ፣ ደስተኛ እና ውጤታማ ቤተሰብ ለመመስረት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ነው።

የክልል ጤና ቢሮ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተገኙበት ይህ አውደ ጥናቱ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው።

በትዕግስት ዘላለም