በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆት አገልግሎት እያስተጓጎለ ነው ተባለ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) ለባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የሀገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እያስተጓጎለ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥራ አስኪያጅ ቡልቱማ ቂጣታ ለባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል የሀገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እያስተጓጎለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 16 ሺሕ 402 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ስርቆት መፈጸሙን ጠቁመው በዚህም  26 ሚሊየን 94 ሺሕ 75 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱን  አስረድተዋል፡፡

አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በልደታ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በለሚኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳምንት ብቻ መሪ ሎቄ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ፣ ልደታ እና ሳሪስ አቦ አካባቢ ከመሬት በታች በተዘረጉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ ስርቆት እና ውድመት መፈፀሙን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተቋሙ እየተባባሰ የመጣውን የባቡር የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆት ለመከላከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም ድርጊቱን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ታሪኩ ማዕረጉ በበኩላቸው በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀምን የስርቆት ድርጊት ለመከላከል የተለያዩ አዋጆች በሥራ ላይ ቢውሉም በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣና ከፍተኛ የሀገር ሃብት እየተዘረፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በሀገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል ብለዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት 11 ወራት በተደረገ ክትትልና የማጣራት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ በቁጥር ከ37 በላይ ‘’የስርቆትና ጉዳት ማድረስ’’ የወንጀል ተግባራት ተፈፅመው ለተለያዩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ክስ ተመስርቶ በምርመራና በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ማኅበረሰቡ ይህን መሰል እኩይ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ሲመለከት በተቋሙ 905 ነጻ የጥሪ ማዕከል ጥቆማ ሊሰጥ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ሊያሳውቅ ይገባል ብለዋል፡፡