ጠ/ሚ ዐቢይ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ለአፍሪካ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክር ጥሪ አቀረቡ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በሰብዓዊ ድጋፍ ለአፍሪካ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው በማላቦ እየተካሄደ በሚገኘው በ15ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ እርዳታ እና ቃል ኪዳን ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጉባኤው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለፁት የአፍሪካ ቀንድ በዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እና በድርቅ ሳቢያ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ከተከሰተበት ቀጠናዎች አንዱ ነው።
ይህንንም የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ከዚህ ቀደም በቀጣናው የተከሰተው ተከታታይ ድርቅ እንደሚያሳየው ጠንካራ የአደጋ መከላከል እርምጃ ወሳኝ እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።
በኢትዮጵያ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ሀገሪቱ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በሚቀጥሉት ጊዜያት በአየር ንብረት ለውጥ ሊመጣ የሚችለውን ፈተናዎች ለመቋቋም የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በዓለም የከፋ የኢኮኖሚ የዋጋ ግሽበት እየታየ ቢሆንም ሀገሪቱ ለዓለም ዐቀፍ ስደተኞች እና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ መስጠቷን አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአኅጉሪቱ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማሳለጥ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ ማቅረባውን ኢቢሲ ዘግቧል።