በአማራ ክልል የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ርክክብ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አዘጋጅነት “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ አርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ርክክብ መርኃ ግብር በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች በክልሉ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ውስንነትን ለመቅረፍና የግብርና ሥራን በዘመናዊ መንገድ በመከወን ምርታማነትን ለማሳደግ  ያግዛሉ ተብሏል፡፡

በተካሄደው ርክክብ ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ አነስተኛ መውቂያ መሳሪያዎች እንዲሁም የውሃ መሳቢያ ፓምፖች እንደሚገኙበትም ነው የተመላከተው፡፡

በዛሬው ዕለት 136 ትራክተሮች በክልሉ ግብርና ቢሮ በኩል ለስርጭት የቀረቡ ሲሆን ከጥር ወር ጀምሮም 324 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ማስተላለፍ መቻሉ በመርኃ ግብሩ ተገልጿል፡፡

በርክክብ መርኃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለን (ዶ/ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና አርሶ አደሮች መገኘታቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡