ለሲሚንቶ የምርትና ግብይት ሰንሰለት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ ነው ተባለ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) በሲሚንቶ ምርት እና የግብይት ሰንሰለት ላይ ለታዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ፤ በሲሚንቶ ምርትም ይሁን የግብይት ሰንሰለት ላይ ችግሮች መኖራቸው የተረጋጋ የሲሚንቶ ገበያ እንዳይኖር እና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በፋብሪካዎች የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ አማካይ መሸጫ ዋጋ 471 ብር መሆኑንና አዲስ አበባ ሲገባ እስከ 1 ሺሕ ብር ድረስ እንደሚሸጥ አንስተው ይህንን ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ ዘርፍ ወደ ማዕድን ሚኒስቴር የገባው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ በፋብሪካዎች የሚታየው የምርት ችግር ምንጩ የተለያየ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ፋብሪካዎች በቂ ሲሚንቶ እንዳያመርቱ የውስጥ ማኔጅመንት ችግር፤ የአካባቢያዊ ሰላም እጦት እና የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አብራርተዋል

ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ እና ተመሳሳይ ጥሬ እቃ የሚጠቀሙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተመሳሳይ የሰው ኃይል ብዛት ኖሯቸው የሚያመርቱትን ምርት ስናይ ትልቅ ልዩነት አለው ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በቀላልና ጥቃቅን የቴክኒክ ችግሮች ምክንያት ሥራ እንደሚያቋርጡ ገልጸው፤ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በሚገኙበት በሆለታ አካባቢ በሚገኝ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የሲሚንቶ ምርት ሥልጠና እንዲሰጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

በሲሚንቶ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ያለው አንዱ በየአካባቢው የሚፈጠረው የሰላም እጦት በመሆኑ ይህን ከክልሎች ጋር በመነጋገር እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በፋብሪካዎች እንዲሠማሩ በማድረግ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን መደረጉን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡