ሕብረቱ ኢትዮጵያን ለመካስና ለመደገፍ አበክሮ እንደሚሰራ አስታወቀ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ሕብረት (UN-ITU) ኢትዮጵያን ለመካስና ለመደገፍ አበክሮ እንደሚሰራ አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ሕብረት ቢሮ ተገኝተው ከህብረቱ ዋና ፀሐፊ ሆሊን ዣዎ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ቀደም ብሎ በተወሰነው መሠረት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ልማት ጉባኤን በሰኔ 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ እንድታዘጋጅ እድሉ ተሰጥቷት የነበረ ሲሆን፤ ይህን ዝግጅት ለማከናወን በተለይ ሚኒስቴሩ የወሰደውን ሀገራዊ ኃላፊነት ተከትሎ በርካታ ዝግጅቶችን ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል።

ሆኖም ከወራት በፊት ከነበረው ሀገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለ ኢትዮጵያ ሲያናፍሱት በነበረው የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም አንዳንድ ሀገራት በወቅቱ በያዙት አቋም ምክንያት ሕብረቱ ለኢትዮጵያ የሰጠውን እድል አንስቶ ለሌላ ሀገር ማስተላለፉ ተገልጿል።

ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ሀገር የተሰጠው እድል ወደ ሩዋንዳ የተላለፈ ሲሆን ሩዋንዳም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ጉባኤውን ታስተናግዳለች።

አጠቃላይ ሂደቱን አስመልክቶ ሚኒስትሩ ዶ/ር በለጠ ኢትዮጵያ የተሰጣትን እድል በስኬት ለማካሄድ በርካታ ዝግጅቶች ስታደርግ የቆየች መሆኗን፤ በሂደቱም ከፍተኛ ጊዜና ሀብት ያወጣች መሆኑንም ገልጸው በተወሰደው ውሳኔ ሀገራቸው እጅጉን ቅር መሰኘቷን ገልጸዋል።

ሆኖም ያለፈውን እንደመማሪያ ወስዶ ሕብረቱ ኢትዮጵያን መካስ በሚያስችለው ሁኔታ ለወደፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ጉባኤዎችን አዲስ አበባ ላይ እንዲያደርግና በተጨማሪም የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ አበክረው ጠይቀዋል።

የሕብረቱ ዋና ፀሐፊም ለሆነው ሁሉ ይቅርታ በመጠየቅ የሚኒስትሩን ጥያቄዎች ተቀብለው ለወደፊቱ ህብረቱ ኢትዮጵያን እንዲክስና እንዲደግፍ አበክረው እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።