የዓለም አካባቢ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገለጸ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) በየዓመቱ ግንቦት 28 የሚከበረው የዓለም አካባቢ ቀን ዘንድሮ “አንድ ምድር ብቻ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገለጸ።
ቀኑ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ እንደሚከበር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የዓለም የአካባቢ ቀን በየዓመቱ ግንቦት 28 እንዲከበር የተወሰነው እ.ኤ.አ በ1972 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የሰው ልጅና አካባቢን የተመለከተ በስቶክሆልም ባካሄደው ኮንፍረንስ ነው፡፡
በዚህም በአዲስ አበባና በጅግጅጋ ከሰኔ 2 እስከ 6 በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ተብሏል።
ከግንቦት 26 እስከ 29 በአዲስ አበባ በወዳጅነት ፓርክ ዕለቱን ታሳቢ በማድረግ አውደ ርዕይ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) የአካባቢ ጥበቃ ቀንን ማክበርና በዚህ አጋጣሚም የሕዝብን ግንዛቤ ማዳበር የዓለም ዐቀፉ ኅብረተሰብ አካል ስለሆንን ብቻ የምንፈፅመው ተግባር አይደለም፤ የአካባቢ ጉዳይ ካደጉት አገራት በላይ የሚያሳስብና የሚያሰጋን ስለሆነ ነው ብለዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን ለመቀነስ ሚዛን የሚደፋ ሚናን ስትወጣ አልነበረም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይሁንና ባለፉት ሦስት ዓመታት ባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃ ላይ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በታምራት ደለሊ