በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባል ተባለ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) በከተሞች አካባቢ የተገልጋዩን ኅብረተሰብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ይገዙ ገለጹ

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በከተማ መሬት እና ፕላን ዘርፍ ከደቡብ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናና የምዘና መርኃ ግብር በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡

በከተሞች የሚካሄደው የአገልግሎት አሰጣጥ የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ውስንነት የሚስተዋልበት መሆኑን የቢሮ ኃላፊው በተለያየ ደረጃ የሚነሳው የሕዝብ ቅሬታ ምላሽ አግኝቶ ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዲያሳልፉ መስራት ይገባል ብለዋል።

በከተሞች ከመሬት ሀብት እና አስተዳደር ጋር የሚያያዙ የአሰራር፣ የአደረጃጀት እና የህግ ማዕቀፍ ክፍተቶችን በመፈተሽ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ሊታገዝ ይገባልም ነው ያሉት።

የባለሙያውን ብቃት በተገቢው መንገድ በመለካት የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻል እንደሚገባም ጠቁመው በሦስቱም ክልሎች የሚገኙ ከተሞቻችንን ለማዘመን እና የተገልጋዩን ማኅበረሰብ ፍላጎት በሟማላት ረገድ የስልጠናው አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል።

እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመታገል የአገልግሎት ፈላጊውን ሕዝብ እርካታ ማሳደግ ይገባል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ካሊድ አብዱረህማን በበኩላቸው የከተሞችን ልማትና እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የከተማው ነዋሪ በሚመኘው እና በሚፈልገው ሁኔታ እንዲለማ እና እንዲደራጅ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በዘርፉ በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን ተናግረዋል።

ለከተማ ልማት ስራ ከሚሰጠው ትኩረት በተጓዳኝ ከመሬት እና መሬት ነክ ንብረት የመረጃ ሥርዓት ክፍተቶች ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ እንዲሁም በዘርፉ የሚያጋጥመውን ሌብነት መመከት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የነዋሪዎችን የመሬት ባለቤትነትና ዋስትናን ለማረጋገጥ የዘርፉን የመረጃ አያያዝ በማዘመን የመሬት መረጃ ሥርዓቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አጀንዳ ከመሆኑም በላይ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያግዛልም ነው ያሉት።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታከለ ታደሰ (ፕ/ር) በ16 የሙያ ደረጃዎች ስልጠና መስጠት እና በደረጃ 5 ብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ ለሚቀጥሉት 45 ቀናት በስልጠና ላይ እንደሚቆዩም ከደብቡ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።