ሕግ የማስከበሩ ሥራ ትኩረት እንዳልተነፈገው አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ተናገሩ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የሕግ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ በመንግሥት በኩል ባለው ተነሳሽነት የተነሳ ሕግ የማስከበሩ ሥራ ትኩረት እንዳልተነፈገው አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካይ ትሬንት ኬሊ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በተለያዩ መንስዔዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው መንግሥት በያዘው በጎ አቋም የተነሳ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ቢሆን ርዳታ የማቀበሉ ነገር ቀጥሏል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ተገቢው ክትትል እና ማጣራት ተደርጎ የሕግ ተጠያቂነት እየሰፈነ መሆኑንም አያይዘው አብራርተዋል።
የሕግ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ በመንግሥት በኩል ባለው ተነሳሽነት የተነሳ ሕግ የማስከበሩ ሥራም ትኩረት እንዳልተነፈገው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላሟን እና አንድነቷን በተሻለ ሁኔታ ጠብቃ ለማቆየትም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቅርቡ መመሥረቷን አፈ-ጉባዔ ታገሠ አስረድተዋል።
ትሬንት ኬሊ በበኩላቸው መልካም የሆኑት ጅማሬዎች ሁሉ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀው ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና ሕግጋት በሙሉ መከበራቸውን መንግሥት እንደሚያረጋግጥ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እና በጋራ ጉዳዮችም ላይ ያተኮረ እንደነበርም የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡