የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፑቲንን ለማግኘት ወደ ሩሲያ ተጓዙ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ነገ አርብ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ያነጋግራሉ ተባለ፡፡

ማኪ ሳል በጦርነቱ ምክንያት በዩክሬን ወደቦች ላይ በቀሩ የምግብ እና የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ግብዓቶች ጉዳይ ላይ ለማውራት ነው ፑቲንን የሚያገኙት፡፡

ማኪ ሳል በፕሬዝዳንት ፑቲን ግብዣ ወደ ሩሲያ ማቅናታቸውን እና በሪዞርት ከተማዋ ሶቺ እንደሚገናኙ ያስታወቀው ጽሕፈት ቤታቸው ነው፡፡

ከሩሲያ መልስ ወደ ጋና አክራ አቅንተው በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ጉባዔ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

ኢኮዋስ በመጪው ቅዳሜ በማሊ፣ በጊኒ እና በቡርኪና ፋሶ በተከሰቱ የመፈንቅለ መንግስት ጉዳዮች ላይ ይመክራል፡፡

ሊቀመንበሩ ከፑቲን ጋር በሚገናኙበት ወቅት በጥቁር ባሕርና በሌሎችም የዩክሬን ወደቦች የሚገኙት ምርቶቹ ወደ አፍሪካ ሊገቡ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡

ጦርነቱን ሊረግብና ሰላማዊ መፍትሔዎች ሊዘየዱ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉም ነው የተባለው፡፡

ማኪ ሳል ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ነው ወደ ሩሲያ ያቀኑት፡፡

ዛሬ ሃሙስ ሞስኮ እንደሚደርሱ የሚጠበቅ ሲሆን ነገ አርብ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አግኝተው ያነጋግራሉ ተብሏል፡፡

የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ትናንት ረቡዕም ከአውሮፓ ህብረት የምክር ቤት አባላት ጋር የበይነ መረብ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ስለ ዩክሬን ጦርነትና ጦርነቱን ተከትሎ ስላጋጠመው የምግብ አቅርቦት ችግር ተነጋግረዋል፡፡

ሩሲያ በመላው ዓለም ያጋጠመው የምግብ አቅርቦት ችግር ከጦርነቱ ጋር ከወሰደቻቸው እርምጃዎች ይልቅ በምዕራባውያኑ ማዕቀብ ምክንያት የመጣ መሆኑን ትናገራለች፡፡

ሆኖም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ሩሲያ ጉዳዩን በመያዣነት እንደወጥመድ እየተጠቀመችበት ነው በሚል ወቅሰዋል፡፡

ማኪ ሳልም አውሮፓ እና አፍሪካ እንደመያዣ መጠቀሚያ ሊሆኑ አይገባም የሚለውን የማክሮንን ሃሳብ ይጋራሉ ሲል አልዐይን ዘግቧል፡፡

የሩሲያ መንግስት ግን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስለ ጉዳዩ ያለው ነገር የለም፡፡