ቱርክ በአዲሱ ስሟ ‘ተርኪዬ’ እንደምትጠራ አስታወቀች

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) ‘ተርኪ’ ተብላ የምትታወቀው ቱርክ በስሟ ላይ ማሻሻያ ማድረጓን ለተባበሩት መንግሥታት አቅርባ ተቀባይነት በማግኘቱ ‘ተርኪዬ’ በሚል እንደምትጠራ አስታወቀች።
እራሷን በዓለም ዙሪያ በአዲስ ገጽታ ለማስተወወቅ የተነሳችው ቱርክ በፕሬዝዳንቷ አማካይነት ባስተዋወቀችው ዘመቻ በስሟ ላይ ያደረገችውን ለውጥ ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ።
ባለፈው ኅዳር ወር ላይ “ተርኪዬ የሚለው ስያሜ የቱርክን ሕዝብ ባህል፣ ሥልጣኔ እና ዕሴቶችን በበለጠ የሚወክል አገላለጽ ነው” በማለት ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ተናግረው ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የስያሜ ለውጡን ጥያቄ በዚህ ሳምንት ከተቀበለ በኋላ፣ ወዲያውኑ ለውጥ ማድረጉን አሳውቋል።
አብዛኞቹ ቱርካውያን አገራቸውን ‘ተርኪዬ’ ብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው ‘ተርኪ’ የሚለው ስያሜ በዓለም ዙሪያ በስፋት ይታወቃል።
የስያሜ ለውጡ ይፋ ከተደረገ በኋላ የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋም የሆነው ‘ቲአርቲ’ ወዲያውኑ ነበር ለውጥ ያደረገው።
ለለውጡ ምክንያት ብሎ ካስቀመጣቸው ነገሮች መካከል ‘ተርኪ’ የሚለው ስያሜ ምዕራባውያን በገና እና በአዲስ በዓል ወቅት ለምግብ ከምትቀርበው የዶሮ ዝርያ ጋር መያያዙ እንደሆነ፣ በተጨማሪም በኬምብሪጅ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ላይ ለቃሉ ተሰጠው ትርጉም እንደሆነም አመልክቷል።
መንግሥት ቱርክን በአዲስ ስያሜ ለማስተዋወቅ በጀመረው ዘመቻ በአገሪቱ ተመርተው ወደ ውጪ የሚላኩ ሁሉም ምርቶች ላይ አዲሱ ስያሜ እንዲሰፍር የተደረገ ሲሆን፣ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮም “ሄሎ ተርኪዬ” የሚል የቱሪዝም ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!