እሁድ በመስቀል አደባባይ ለሚካሄደው የምስጋና እና የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም የሚዘጉ መንገዶች ይፋ ሆኑ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ የፊታችን እሁድ ዕለት በመስቀል አደባባይ ለሚካሄደው የፖሊስ አመራር እና አባላት የምስጋና እና የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም የሚዘጉ መንገዶችን ይፋ አድርጓል።
በሀገራችን በተካሄደው የሕግ ማስከበር፣ የኅልውና እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻዎች እንዲሁም በሌሎች ፖሊሳዊ ሥራዎች ጀግንነት ለፈፀሙ እና የላቀ የሥራ ውጤት ላስመዘገቡ አመራር እና አባላት የምስጋና እና የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም “በመሥዋዕትነታችን የሀገራችን አንድነት እና የሕዝባችን ሰላም ይረጋገጣል” በሚል መሪ ቃል እሁድ ግንቦት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በመስቀል አደባባይ በታላቅ ድምቀት እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
በመሆኑም ሥነ-ሥርዓቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት፦
• ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር (ኦሎፒያ አደባባይ)
• ከመገናኛ፣ በ22 ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድኃኔዓለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያ አካባቢ በላይና በታች
• ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ገብርኤል መሳለሚያ አካባቢ
• ከቸርችል ጎዳና በሐራምቤ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ፖስታ ቤት
• ከተክለሀይማኖት በሚቲዎሮሎጂ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሚቲዎሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ
• ከተክለሀይማኖት፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወደ ኢሚግሬሽን የሚወስደው መንገድ ጥቁር አንበሳ የኋላ በር
• ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ለከባድ መኪና አጎና አካባቢ ለቀላል መኪና የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር
• ከጦር ኃይሎች፣ ልደታ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ሜክሲኮ አደባባይ
• ከሜክሲኮ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ለገሃር መብራት
• ከሰንጋ ተራ በቴሌ ባር ለሚመጡ አሽከርካሪዎች በድሉ ሕንፃ አካባቢ
• ከንግድ ማተሚያ ቤት በውስጥ ለውስጥ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦርማ ጋራዥ አካባቢ
• ከሸራተን ወደ አምባሳደር ለሚመጡ ፍል ውኃ አካባቢ
• ከካዛንቺስ ወደ ፍል ውኃ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አካባቢ
ቅዳሜ ለዕሁድ አጥቢያ ከለሊቱ 10፡30 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ መሆናቸውን ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት መሠረት አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።