የቱርክ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ቢመጡ መንግሥት ለመደገፍ ዝግጁ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) የቱርክ ባለሃብቶች ያላቸውን እውቀት፣ ልምድና ክህሎት ተጠቅመው ወደ አማራ ክልል ኢንቨስት ለማድረግ ቢመጡ የክልሉ መንግሥት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ የተመራ ልዑክ ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኢንቨስትመትና ሌሎች ተያያዠ ጉዳዮች ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ መክረዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የቱርክ ባለሃብቶች በክልሉ በኢንቨስትመንትና በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ እየተሳተፉ ነው።

የዓባይ ድልድይ ግንባታ ላይ በማማከር፣ በምስራቅ አማራ እየተገነባ ባለው የባቡር መንገድ በተቋራጭነትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል በእርሻ፣ በማዕድን፣ በጨርቃጨርቅ፣ በቱሪዝምና ሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች እምቅ ሃብት ያለው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።

ቱርክ በፊልም፣ በሙዚቃና ሌሎች የባህል ልማቶች ሰፊ ልምድ ያላት አገር በመሆኗ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ በበኩላቸው በርካታ ባለሃብቶች በአማራ ክልል በኢንቨስትመንት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በጨርቃ ጨርቅ፣ በጥጥ ልማት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታና በሌሎች ዘርፎች በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣይም አሁን ያለውን መልካም የግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንሰራለን ሲሉ አምባሳደሯ አስረድተዋል።