ከ2015 የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙ ተገለጸ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮን ብር ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ተናገሩ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌዴራል መንግሥት የ2015 ዓ.ም ረቂቅ የበጀት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

ረቂቅ የበጀት እቅዱን ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ረቂቅ በጀቱ የተዘጋጀው ከባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የረቂቅ በጀቱ ዝግጅት በ2014 በጀት ዓመት የነበሩ አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታዎችና የቀጣይ ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት እንደሚያሳይና አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታው ሰላማዊ እንደሚሆን ታሳቢ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

የ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የተያዘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 218 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለካፒታል በጀት መመደቡን ጠቅሰዋል፡፡

345 ነጥበ 1 ቢሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ፣ 209 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ደግሞ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንደሚከፋፈልም አብራርተዋል፡፡

ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል ነው ያሉት፡፡

ከተመደበው በጀት ውስጥ 400 ቢሊዮኑን ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ገልጸው ይህም ከ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ36 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ምክር ቤቱ በቀረበው የረቂቅ በጀት በስፋት ከመከረ በኃላ የረቂቅ አዋጅ ቁጥር 8/2014 ሆኖ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ በመምራቱም ታውቋል።