በሀረሪ 3ኛው ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ተጀመረ

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል በሦስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባት 80 ሺሕ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎችን ለመከተብ ታቅዶ መሰጠት ተጀመረ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈቲህ መሃዲ በክልሉ በሁለት ዙሮች በተካሄደ የክትባት ዘመቻ ከ109 ሺሕ በላይ የክልሉ ነዋሪዎችን መከተብ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በሽታውን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

በክልሉ በሦስተኛው ዙር በሚሰጠው የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻም እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑና ከ80 ሺሕ በላይ ዜጎችን ለመከተብ መታቀዱን ተናግረዋል።

ክትባቱን መውሰድ በሽታውን አስቀድሞ ከመከላከል አንፃር ጉልህ ሚና ስለሚኖረው በተለይም አቅመ ደካሞች እና የጎንዮሽ ጉዳት ያለባቸው ዜጎች ክትባቱን መውሰድ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ለክትባት ዘመቻው ውጤታማነትም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ተስፋየ ኃይሉ (ከሀረር)