በአጎራባች ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ማስፈንን አላማ ያደረገ ምክክር በሀዋሳ እየተካሄደ ነው

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የአጎራባች የመንግሥታት ግንኙነት መድረክ ዛሬ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።

በክልሎቹ መካከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በጋራ ለመፍታት፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን በጋራ ማረጋገጥ የመድረኩ ዓላማ ሲሆን በመድረኩ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማትን ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።

በመድረኩ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመገንባት ይቻል ዘንድ ከተናጠል ጥረቶች የጋራ አቅሞች በተገቢው መንገድ አቀናጅቶና አዋኅዶ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል ፎረም ይመሰረታል ተብሎም ይጠበቃል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባዘጋጀው በዚሁ የምክክር መድረክ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሃራ ሁመድ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ይገዙና የየክልሎቹ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችና ተወካዮች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW