ኢጋድ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለጸ

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የትምህርት ጥራት በአካባቢው አገራት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለጸ።

ኢጋድ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ለሚያስተምሩ መምህራን የሁለት ቀናት የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአዲስ አበባ አስጀምሯል።

በሥልጠና መርኃ ኃብሩ ከኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ሱዳን የተውጣጡ 45 ሠልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለአንድ ዓመት በሚቆየው የሥልጠና ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ የተውጣጡ 607 መምህራን ሥልጠናውን አግኝተዋል።

ከኢትዮጵያ 206፣ ከሱዳን 201 እንዲሁም ከኡጋንዳ 200 መምህራን በሁለት ዙር ሥልጠናውን ተከታትለው ማጠናቀቃቸው ተጠቁሟል።

ሥልጠናው በዋነኛነት የሥርዓተ-ትምህርት፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ በህይወት ክህሎትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ትኩረት አድርጓል። ሥልጠናው በቀጣይ በደቡብ ሱዳን፣ በጂቡቲና በኬኒያ እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።

የኢጋድ የጤናና ማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ፈቲያ አልዋን እንደገለጹት ኢጋድ በቀጣናው አገራት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው።

በተለይም የስደተኛ ልጆች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙና በያሉበት አገር የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲዋሃዱ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢጋድ የትምህርት፣ ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ከፍተኛ አስተባባሪ ከበደ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎች በሥነ-ልቦና ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ሥልጠና በተማሪዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማስመዘግቡንም ነው የገለጹት።