ጠ/ሚ ዐቢይ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገለጹ

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንደሚጠናክሩ ያላቸውን እምነት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ ማህሙድ በዓለ ሲመት ላይ በሞቃዲሾ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በሶማሊያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የጋራ እድገት እና ልማት ትብብር ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመከተሏ ሁለቱ አገራት በቀጣናዊ ትስስር አዲስ መንገድ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገኙ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ከአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር በጋራ በመስራት ይበልጥ እንደሚጠናከሩ እና እንደሚሰፉም ነው ያስታወቁት።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ሥራቸው የተሳካ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደምታደርግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታውቀዋል።

ያለጎረቤቶቻችን ትብብርና ድጋፍ በተናጠል ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ ባህላቸውን፣ ደኅንነታቸውንና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ብልጽግናን እንደሚያረጋግጡም ጠቁመዋል።

ኤፍቢሲ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ንግግራቸው ለፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ የተሳካ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በበኩላቸው በኢኮኖሚ ጠንካራ እና ሰላሟ የተረጋገጠ ሶማሊያን ለመፍጠር እንሰራለን ብለዋል።

“ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራትና ከመላው ዓለም ጋር ጠንካራ ትብብር እንመሰርታለን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ የትብብር መስኮችም ንግድ፣ ኢኮኖሚና ሽብርተኝነትን መዋጋት እንደሚሆንም አመላክተዋል።