በሸኔ ታጣቂ ኃይል ጉዳት የደረሰበት የመልካ ጉባ ድልድይ ተገንብቶ ተጠናቀቀ

የመልካ ጉባ ድልድይ

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) በሽብርተኛው የሸኔ ታጣቂ ኃይል ጉዳት የደረሰበት የመልካ ጉባ ድልድይ መገንባት ዘርፈ ብዙ ወታደራዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በቦታው የሚገኙ የፀጥታ ተቋማት አመራሮች ተናግረዋል።

የድልድዩ መሰራት ሰራዊቱ በዳዋ ወንዝ ሙላት ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ግዳጅ ለመፈፀም የነበረበትን ተግዳሮት የፈታ የግንባታ ሂደት መሆኑም ተጠቅሷል።

በደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ብርሃነ ልጃለም ከዚህ ቀደም የሸኔን ታጣቂ ኃይል ለመደምሰስ በተደረገው ዘመቻ የዳዋ ወንዝ ከፍተኛ ለተልዕኮ ችግር እንደነበር አውስተው የድልድዩ ግንባታ ፈጣን፣ ተወርዋሪና በሁሉም ቀጣናዎች ተንቀሳቅሶ ለድል የሚበቃ ሰራዊት የመገንባት አንድ አካል ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።

በዕዙ የሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ገበረ ጋሞ ግንባታው የሰራዊታችን ድካም በመቀነስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተልዕኮን በብቃት የመወጣት ሥራ የሚያቀላጥፍ ከመሆኑ ባሻገር የሶማሌና የኦሮሚያ አጎራባች ሕዝቦችን ልማታዊ ትስስር የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የሬጅመንት አዛዥ ኢንስፔክተር ጅብሪል አደም በበኩላቸው ለዓመታት አስቸጋሪ የመሬት ገፆችን እንደምሽግ በመጠቀም የሽብር ሥራውን ሲያከናውን የቆየውን የሸኔ ቡድን ለመደምሰስ ቅንጅታዊ ሥራ ተግባራዊ መደረጉ ለተገኘው ድል ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ጠቁመዋል፡፡

በዘመቻው ወቅት ፈተና የነበረው የዳዋ ወንዝ ሙላት አሁን ላይ በተረጋገጠው ሰላም የድልድይ ግንባታ ተሰርቶለት መላው የፀጥታ ኃይል ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ መደረጉን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገነባው ይህ የብረት ድልድይ የሶማሌ ክልል ዳዋ ዞንን እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጅና ቦረና ዞኖችን የሚያዋስን መሆኑን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!