ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረት ለኢኮኖሚ ሪፎርሙ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገለጸ

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረት ኢትዮጵያ ልታሳካ ላሰበችው የኢኮኖሚ ሪፎርም አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ተገለጸ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፣ የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የፌዴራል አመራሮች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማስጀመር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከድሬዳዋ ካቢኔ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ነፃ የንግድ ቀጣናው ድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም ዐቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት የሚገባ ይሆናል ብለዋል፡፡

ይህም እንደ ሀገር የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጥ የሚችል መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያን የገቢና ንግድ ሥርዓት በማሳለጥ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች መንግሥት በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመስረት መነሳቱ ሀገሪቱ ልታሳካ ላሰበችው የኢኮኖሚ ሪፎርም አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ሚኒስትሯ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር እና የካቢኔ አመራሮች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመስረት መንግሥት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው ለተግባራዊነቱ ከፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡