ሞዛምቢክ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆነች

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) ሞዛምቢክ 192 የፀጥታው ምክር ቤት አባላትን ድምፅ በማግኘት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆናለች፡፡

ከሞዛምቢክ በተጨማሪ ኢኳዶር፣ ጃፓን፣ ማልታ እና ስዊዘርላንድ ትላንት በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ምርጫ የአባልነት እውቅና የተሰጣቸው ሀገራት ናቸው፡፡

ትላንት በተደረገው የፀጥታው ምክር ቤት የአባልነት ምርጫ ሞዛምቢክ 192፣ ኢኳዶር 190፣ ጃፓን 184፣ ማልታ 185 እና ስዊዘርላንድ 187 ድምፅ በማግኘት ነው አባል መሆን የቻሉት፡፡

የሞዛምቢኩ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ በሰጡት አስተያየት ሀገራቸው ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ጥረት ለሚያደርጉ የአፍሪካ ሀገራት በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ድምጽ ትሆናለች ብለዋል።

“ይህ ለሀገራችን ታሪካዊና ሀገራችን ልትኮራ የምትችልበት ወቅት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡

ሞዛምቢክ የግጭትን የማስወገድ እርምጃዎችን የማበረታታት ልምድ አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ ከሁሉም በላይ የሰላም ድርድር መፍትሄዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ሞዛምቢክ የማይናወጥ አቋም እንዳላት ቢቢሲ አፍሪካን ጠቅሶ ኤፍቢሲ ዘግቧል።

15 አባላት ያሉት የመንግሥታቱ የፀጥታው ምክር ቤት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ቻይና በቋሚ አባልነት ያቀፈ ሲሆን ሌሎች ቋሚ ያልሆኑ 10 መቀመጫዎች እንዳሉት ይታወቃል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW