በክልሉ ከ4 ሺሕ በላይ ሕገ ወጥ የሠራተኞች ቅጥር ተሰረዘ

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል 4 ሺሕ 155 ሕገ ወጥ የሠራተኛ ቅጥር፣ ዝውውር ምደባና ደመወዝ መሰረዙን የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዘይኔ ቢልካ እንደገለጹት በመጠናቀቅ ላይ ባለው በ2014 በጀት ዓመት የ25 ሺሕ 990 የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ፋይል ተመርምሮ 4 ሺሕ 155 ሕገ ወጥ የቅጥር፣ ዝውውር፣ ምደባና የደመወዝ ማስተካከያ ሥራዎች ተሰርዘዋል።

በተደረገው የሠራተኞች ፋይል ማጣራት ከ614 በላይ ሰራተኞች በሀሰተኛ የትምህርትና የብቃት ማረጋገጫ ሰነድ ተመርምሮ ቅጥራቸው መሰረዙን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ በአሰራር ችግሮች ሊባክን የነበረ 82 ሚሊየን 887 ሺሕ 682 ብር ማዳን መቻሉንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የሠራተኛው የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲሻሻሉ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል መደረጉንም መናገራቸውን የደሬቴድ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW