ፕሬዝዳንት ፑቲን ሀገራቸው ታሪካዊ ግዛቶቿን እንደምታስመልስ እርግጠኛ መሆናቸውን ገለጹ

ፕሬዝዳንት ፑቲን

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዘመናዊቷ ሩሲያ ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው የቀድሞ ግዛቶቿን በመመለስና ማጠናከር መሆኑን አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ በወጣቶች ስብሰባ ላይ የሀገራቸውንና የዓለምን ሁኔታ በተመለከተ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሩሲያ ታሪካዊ መሬቷን እንደምታስመልስና ይህንንም እንደምታጠናክር አስታውቀዋል።

ሀገራቸው የቀደመ ግዛቶቿን እንደምታስመልስ እርግጠኛ መሆኗን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ስለሀገራቸው ኢኮኖሚም ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል።

ሩሲያ ዝግ ሀገር እንደማትሆን የገለጹት ፑቲን የዋጋ ንረት ምዕራባዊያን በስህተታቸው ያመጡት እንደሆነም ነው ያስታወቁት።

የሩሲያ ንጉሰ ነገስት የነበሩትና የሩሲን ግዛት ያጠነከሩት ፔተር ዘግሬትን ያስታወሱት ፑቲን የዘመናዊቷ ሩሲያ ዕጣ ፋንታ ከቀደመው ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ያለው የዋጋ ንረት የተከሰተው በምዕራባዊያን ስህተት ምክንያት እንደሆነ ያነሱት ፑቲን እነሱ ሌሎች ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ ሲሉም አመልክተዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ጀመርኩት ያለችው “ወታደራዊ ተልዕኮ” የሚጠናቀቀው ግቡን ሲመታ መሆኑን አስታቀውቃለች።

የሩሲያ ቤተ መንግሥት (ክሬምሊን) ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለተልዕኮው አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች መዘርዘራቸውን ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ሩሲያ ወታደራዊ ተልዕኮ እያደረገች መሆኑን ብትገልጽም ምዕራባዊያን ግን ሩሲያ ዩክሬንን እንደወረረች እየገለጹ ሲሆን ሁለቱ አገራት ጦርነት ውስጥ ከገቡ 100 ቀናት ማለፋቸውን የአልዐይን ዘገባ አስታውሷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW