የኢትዮጵያና ሩሲያ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ሰኔ 6/2014 (ዋልታ) መተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሠረተው የኢትዮ-ሩስያ ወዳጀነት በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በክብር እንግድነት በተገኙበት በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ግቢ ውስጥ የተከበረውን የሩሲያ ቀን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ታሪካዊ ግኑኙነትና ጠንካራ ወዳጅነት አሁንም በዘርፈ ብዙ ትብብሮች ታጅቦ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትሩ የሩሲያ ሕዝብና መንግሥት በትምህርት፣ በዕዳ ስረዛ እና በተለይም በአስቸጋሪ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ይቭጌኒ ተርኪን በበኩላቸው የኢትዮጵያና ሩሲያ ታሪካዊ ግኑኙነት ተጠናክሮ ወደ ላቀ ትብብር እንዲሸጋገር የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ገልፀው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሩሲያ መንግሥትና ሕዝብ ላሳዩት አጋርነትና ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW