ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲረባረብ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ

ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲረባረብ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ።

በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ውጤታማ ለማድረግ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በዘንድሮው አመት የሚከናወነው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ የተሳካ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በመድረኩም ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አመራሩ በተለይም የአቅመ ደካማ ወገኖች ቤት የማደስ፣ ማዕድ የማጋራት ሥራ መስራት እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መስራት አስፈላጊ ነው።

በተለይም በክልሉ በዘንድሮው አመት የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

መርኃ-ግብሩ በተለይም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ እና በአሁኑ ወቅት እየተሰተዋለ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ጫናን ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በመሆኑም አመራሩ በላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ከመትከል ባለፈ መንከባከብና እንዲፀድቅ ማድረግ ያስፈልጋል ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው ባለፉት አመታት በዝግጅት ምዕራፍ በቂ ዝግጅት አለመደረጉ በፅድቀት መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዘድሮው ይህንን ክፍተት በሚቀርፍ መልኩ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ለዚህም በአሁኑ ወቅት የፅድቀት መጠንን በሚያሳድግ እና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራን በሚያጠናክር መልኩ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ በተለያዩ ወረዳዎች እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በዘንድሮው ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 70 በመቶው ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በመድረኩም ኅብረተሰቡ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ግንዛቤ የማስፋት ሥራ በትኩረት ማከናወን ይገባል፤ ሕዝቡን በማነቃነቅም በክልሉ በዘንድሮው አመት የታቀደው እቅድ እንዲሳካ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ተነስቷል።

በክልሉ በዘንድሮው አመት 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግሮች ኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ችግኞች በክልሉ ሶፊና ኤረር ወረዳዎች የሚተከሉ መሆናቸውን ተገልጿል።

ተስፋዬ ሀይሉ (ከሀረር)