ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ አሸባሪዎችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ

ሰኔ 13/2014 (ዋልታ) አሸባሪዎችን እና ጽንፈኞችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

አሸባሪውና ፅንፈኛው ቡድን በፀጥታ አስከባሪ አካላትና በሕዝቡ የተባበረ እርምጃ በደረሰበት ሽንፈትና ኪሳራ በአፀፋው የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቅርብ ጊዜ በጋምቤላ አካባቢ ያደረገው ሙከራ ሲከሽፍበት በምዕራብ ወለጋ በጊምቢ አካባቢ ደግሞ በንፁሃን ዜጎች ላይ በተለይም በህጻናትና በሴቶች ላይ ያካሄደው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ እና ኢሰብዓዊ ነው ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ቡድኑ በወሰደው እኩይ የጥፋት እርምጃ ምክንያት በንፁሃን ወገኖች ላይ ለደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው በመንግሥት በኩል የሕግ ማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ተጎጂ ቤተሰቦችን የማረጋጋት፣ የመደገፍ እና መልሶ የማቋቋም ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን እንዲሁም አሸባሪዎችን እና ጽንፈኞችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡