በንጹሃን ላይ የሚፈጸም ግድያ የተሸናፊዎች ድርጊት ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ

ሰኔ 13/2014 (ዋልታ) ከሰሞኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በንጹሃን ላይ የተፈጸመው ግድያ የተሸናፊዎች ድርጊት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

በኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በፌዴራልና በክልል መንግሥት እየተወሰደ ባለው ኦፕሬሽን አሸባሪ ቡድኖች ጥቃቱን መቋቋም ተስኗቸው ተበታትነዋል ብለዋል።

ይሁን እንጅ እነዚህ ተሸናፊ ኃይሎች ሽንፈታቸውን ላለመቀበል የፈሪ ዱላቸውን በንጹሃን ላይ አሳርፈዋል ነው ያሉት።

ይህን እኩይ ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎችን በዘላቂነት ማጥፋት የምንችለው በጋራ ስንቆም ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በዚህ የፈሪ የሽብር ድርጊት ሳንደናገጥ ተባብረን መቆም አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያ በየትኛውም ፈተና ውስጥ አልፋ እንደ ሀገር ጸንታ ትቆማለች ያሉት ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ የስኬት መንገድ በፈተና የተሞላ መሆኑን በመገንዘብ ማንኛውንም ዋጋና መስዋእትነት ከፍለን የኢትዮጵያን ሰላም እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡

በዙፋን አምባቸው