የአረንጓዴው ካባ አብዮት!

በአንድ ወቅት አይንን በሚማርኩ እጽዋት ተውበው የነበሩ ተራሮች ተፈጥሯዊ ጋቢያቸውን አጥተዋል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ማርምን እና ስጋምን በጉያቸው ሸሽገው የያዙ ደኖች በብዙ የሀገሪቷ ክፍል ታሪክ ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡ ሸንተረሮችም ከውሃ ፏፏቴ ከተራራቁ ውለው አድረዋል፡፡

ከሦስት አስርተ ዓመታት በፊት ከ1.1 ሚሊየን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ከሚዘልቀው የሀገሪቷ ቆዳ ስፋት ውስጥ አርባ በመቶው በደን የተሸፈነ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ክፍለ ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ ግበርና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር መሸከም እያቃተው ዜጎች በተደጋጋሚ ጊዜ ለድርቅ ተጋልጠዋል፡፡

ባለፉት ሦሰት አስርተ ዓመታት እንኳ የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ያደገ ሲሆን ሕዝቡን ለመመገብ የእርሻ ቦታዎች ተደጋግመው ከመታረሳቸው በተጨማሪ አዲስ መሬት እየተመነጠረ ለእርሻ ሥራ እንዲውል ሁኔታው አስገድዷል፡፡ መሬቱ በተደጋጋሚ ጊዜ በመታረሱ ለምነቱን እንዲያጣ ብቻ ሳይሆን እንዲከላ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳ የዜጎች በልቶ የማደር እድል ብቻ ሳይሆን የትውልድ ቀጣይነትም እያደር ጥያቄ ውስጥ እየገባ መጣ፡፡

ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት ዜጎች በተናጠልም በጋራም የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መስራት እዲጀምሩ መንግሥት ጥረት አደረገ፡፡ ይህ ጥረት የሀገሪቱን የደን ሀብት እንዲያስራራ ምክንያት ሆነ፡፡

ሀገሪቱ አዝጋሚ በሆነ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ውስጥ ሳለች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን መጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ አጭር ጊዜ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን የአስተዳዳራቸው ዋና መገለጫዎች መከከል አንዱ በማድረግ ወደ ሥራ ገቡ፡፡

አረንጓዴ አሻራ ብለው የጀመሩት ሥራ በተቀናጀና ለዓለም ምሳሌ በሚሆን መልኩ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በመላ ሀገሪቱ እንዲካሄድ ከማድረግም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ፊት አውራሪ በመሆን ሥራው ከሀገር አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰፋ አድርገዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ካባ የማልበሱን አብዮት በተቀናጀ መንገድ እንዲካሄድ ለማስቻል ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ችግኝ የሚተከልበትን ጉድጓድ ቁፋሮ በትኩረት መርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ የችግኝ ተከላውን ሥራ በበላይነት ከመምራት አልፈው የተከላ ሥራው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ተገኝተው በይፋ ከማስጀመር አልፈው ችግኝ ሲተክሉም በተደጋጋሚ አስተውለናል።

በመጀመሪያው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በ2011 ዓ.ም ሲጀምር ብዙዎች ሥራው የአንድ ወቀት ዘመቻ አድርገው አይተውት ነበር፡፡

በወቅቱ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ሥራው የተጀመረ ሲሆን ከእቅድ በላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል። ከግብርና ማኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ 23 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳትፈዋል።

“40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ  ከ353 ሚሊዮን 633 ሺሕ በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ በየዓለም ክብረ ወሰን እንድትይዝ ማድረግ ተችሏል።

በሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ደግሞ በ2012 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ ስድስት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታስቦ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል። በዚህኛው ዙር ከሀገር በቀል ዛፎች በተጨማሪ የፍራፍሬ ተክሎች እና ቡና ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን 80 በመቶ የሚሆኑ ችግኞች መጽደቃቸው ተነግሯል።

ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሀሳብ በ2013 ዓ.ም ተተግብሯል፡፡ በዚህም ስድስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ መትከል መቻሉ ይታወሳል።

ሦስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ሀገሪቱን አረንጓዴ ካባ የማልበሱ አብዮት ከሀገር አልፎ ወደ ጎረበት ሀገራት መስፋፋቱ ነው፡፡ በወቅቱ አንድ ቢሊየን ችግኝ በጎረቤት ሀገራት እንዲተከል ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሥራ ባልደረቦቻቸው በአንደኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተጠራጠሯቸውን ኢትዮጵያውያን እና የሌሎችን ሀገራት ዜጎች ጭምር አሳምነው እነሆ ለአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ነገ ሰኔ 14/2014 ዓ.ም በይፋ ሊያስጀምሩ ነው።

በዚህኛው  ዙር ደግሞ ከ6 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለደን የሚሆን  2 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ለጥምር ደን የሚውሉ ችግኖች ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 518 ሚሊዮኑ የፍራፍሬ ችግኝ፣ 35 ሚሊዮን ቀርከሃ፣ 800 ሚሊዮን ለእንስሳት መኖ ጥቅም የሚሰጡ ቁጥቋጦዎች እና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞች ናቸው።

በአራቱ ዓመታት ኢትዮጵያን አረንጓዴ ካባ የማልበስ አብዮት 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ቢታቀድም ባለፉት ሦስት መርኃ ግብሮች ብቻ ከ18 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በሦስቱ ዙር የተተከሉ ችግኞች አማካኝ የመጽደቅ ደረጃ ከ80 በመቶ በላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡

እናት ሀገር ኢትዮጵያን በአረንገዴ ካባ የማልበሱ አብዮት በዚሁ ከቀጠለ በኢትዮጵያውያን ላይ ያንዣበበውን የአካባቢ መደህየት በመመከት የትውልድ  ቀጣይነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የጠፋውም ፏፏቴ ይመለሳል፡፡ ደኑም እንደ ወትሮው ማርና ስጋን በጉያው አቅፎ እንካችሁ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውም ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋም ያኔ ሳይወድ በግዱ እጁን ይሰጣል፡፡