የአፍሪካ-እስያ የፓርላማ ጉባዔ እየተካሄደ ነው

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ-እስያ ሀገራት የፓርላማ አባላት የትብብር ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ዛሬ የተጀመረው ጉባዔው ከአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ለተወጣጡ የፓርላማ አባላት በሥነ-ሕዝብ እና የልማት ጉዳዮች እንዲሁም ምክር ቤታዊ ተግባራትን ከመወጣት አንጻር እየመከረ ነው ተብሏል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ደሳለኝ ወዳጆ ለጉባዔው ድጋፍ ያደረጉ የእስያ ሀገራትን አመስግነዋል።

በጉባዔው አማካይነትም የ2030 የዕድገት እና የልማት ዕቅድ በተለይም የትምህርት፣ የመሠረተ-ልማት እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

እንደዚህ ዓይነት ጉባዔዎች ምክር ቤቶች የጋራ መማማሪያ መድረክ እና አጋዥ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ጉባዔው ምክር ቤቶች ለሚያደርጉት የሰላም፣ የደኅንነት እና የዕድገት ተግባራት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተገልጿል።

ለዚህ የጋራ ምክክር ድጋፍ ያደረጉትን በእስያ የጃፓን ትረስት ፈንድ እና የእስያ ሥነ-ሕዝብ እና ልማት ማኅበር መሆናቸውን መባሉን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።