በመዲናዋ ደንብን ከተላለፉ ግለሰቦች ከ28 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ

ሰኔ 15/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ደንብን ከተላለፉ ግለሰቦች በቅጣት እና በውርስ በ11 ወራት ውስጥ ብቻ ከ28 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር፣ መከላከል እና መቆጣጠር እርምጃ አወሳሰድ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ፉፋ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተያዙ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ካሬ መሬት በላይ በማስለቀቅ ለመሬት አስተዳደር ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡

የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ጋር “ደንብን ለማስከበር ደንብ እናክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ምክክር አድርጓል፡፡

በመዲናዋ በሁሉም መስኮች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅድሚያ ደንብ አስከባሪዎች የወጡ ደንብ እና ህጎችን ማክበር እንዳለባቸውም የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ተናግረዋል፡፡

ደንብ አስከባሪዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለሀገርና ለሕዝብ ዘብ መቆም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፎችን ለመግታት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት