የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብርናን ማዘመን አማራጭ የሌለው ተግባር ነው

ሰኔ 16/2014 (ዋልታ) “የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብርናን ማዘመንና ማሻገር አማራጭ የሌለው ቀዳሚ ተግባራችን ነው” ሲሉ በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አብዱረህማን አብደላ ገለጹ።
የክልሉን ግብርና ከመሰረቱ ለመለወጥ ያስችላል የተባለ የኦሮሚያ የግብርና ክላስተር ሽግግር ምክር ቤት ዛሬ ተመስርቷል።
ግብርና በአሁኑ ወቅት የሀገሪቷ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ያሉ ሲሆን አሁን ባለንበት ሁኔታ የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ አንችልም ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ለግብርና ሽግግር ወሳኝ መሰረት የሚሆኑ 17 የተለያዩ መርኃ ግብሮች ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ በመስኖ ስንዴ፣ በቢራ ገብስ፣ በጤፍ፣ ቦቆሎን ጨምሮ በኤክስፖርት አቮካዶ፣ በቡናና ሻይ፣ በሙዝ ልማት፣ በማር፣ በእንስሳትና ሰብል ልማት ሥራ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
የተቀረፁትን የግብርና ሥራ ግቦችን ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ ግብርና ክላስተር ሽግግር ምክር ቤት ዛሬ በይፋ መመስረቱን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በክልሉ የሚገኙ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩቶችን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሴክተሮችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮማያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አበራ ወርቁ በበኩላቸው በዘንድሮው ዓመት ብቻ 6 የሚሆኑት መርኃ ግብሮች እየተተገበሩ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተቋቋመው የግብርና ክላስተር ሽግግር ምክር ቤት ባለድርሻ አካላትን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ርብርብ እንዲያደርጉ ለማስቻል ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
በምክር ቤቱ ምስረታ ላይ በክልሉ በግብርና ዘርፍ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላትና ተመራማሪዎችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ሴክተሮች አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።