የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባላት የሕግ ማስከበር እርምጃው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት ያጸና ነው አሉ

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባላት

ሰኔ 16/2014 (ዋልታ) በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት ያጸና መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ገለጹ።

በአሸባሪው ሕወሓትና ተላላኪዎች ተልዕኮ አስፈጻሚነት የተደራጁ የሽብር ቡድኖች በለወጡ ማግስት ሀገራዊ ቀውስና ትርምስ እንዲፈጠር ሲታትሩ መቆየታቸውን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ተናግረዋል።

ከፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ተመስገን ጥሩነህ፣ ሐጂ አወል አርባ፣ መለስ አለሙ እና ሳዳት ነሻ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ሲፈትኑ ከነበሩ ፈተናዎች ጀርባ የሕወሓትና ተላላኪዎች እጅ ነበረበት ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ዝርፊያና ንብረት ውድመት፣ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች፣ የንጹሃን ጥቃቶች በመፈጸም አሸባሪው ቡድን ቀደም ብሎ በዘረጋው ውስጣዊና ውጫዊ መረብ ዋናውን ድርሻ ወስዷል።

በዚህም ላለፉት ዓመታት በየጊዜው ተለምዷዊ የመሰሉ መልከ ብዙ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች እየተከሰቱ ሕዝቡን ለሞት፣ ለንብረት ውድመትና ለመፈናቀል እንደዳረጉ ገልጸው በሌላ በኩል በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እገታና ሌሎች ወንጀሎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ በኋላ አንገብጋቢው ሕዝባዊ ጥያቄ በሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር በመሆኑ፣ መንግሥትና ፓርቲው በሕዝብ ጥያቄ መሰረት በተወሰደው ሕግና ሥርዓት የማስከበር እርምጃ ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከአሸባሪው ሕወሓት ወረራ በኋላ በተፈጠሩና ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ስጋት የሆኑ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ ስርቆት፣ ዝርፊያና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ መቀነሱን ተናግረዋል።

ከጸጥታ ኃይሉ የከዱ፣ ከማረሚያ ቤቶች ያመለጡ እና በነፍስ ግድያ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በሕገ-ወጥ አደረጃጀቶች ውስጥ እንደነበሩበትም ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ የወረራቸው ቦታዎች የማስለቅቅ እና ሕዝቡን በተለቀቁ ቦታዎች አደረጃጀቱን እንዲያጠናክር በማድረግ የተሰራውንም ጠቅሰዋል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ እርምጃ ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት መረጋገጡን፣ በኑሮ ውድነት ጫናውን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በሕግ ማስከበር እርምጃው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ፈተናዎች እፎይታ የሰጠ፣ በሕዝብና መንግሥት መካከል መተማመን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡም ከጸጥታ ኃይሉ እና ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የተጠናከረ ትብብር ያደረገበት አጋጣሚ እንደነበር አንስተዋል።

የሕዝብ ሰላምና ፀጥታ እየተመዘገበ ባለበት ሁኔታ ከሰሞኑ አሸባረው የሸኔ ቡድን ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ መግደሉን ጠቅሰው ይህም የአሸባሪ ቡድኑን ቀቢጸ ተስፋ ማሳያ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአንድ ሀገር የልማት ሥራ ሰላም ከሌለ እውን ስለማይሆን ሰላምና ጸጥታን የማረጋገጥ ጉዳይ በቀጣይም በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላት አረጋግጠዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW