ደብረ-ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨማሪ ትኩረት ያስፈልጋታል ተባለ

ሰኔ 17/2014 (ዋልታ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ደብረ-ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨማሪ ትኩረት እንደሚያስፈልጋት ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው በደብረ-ብርሃን ከተማ የሚገኝ በውስጡ ስምንት ሼዶች ያቀፈውን የኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል፡፡
ኮሚቴው በፓርኩ ውስጥ የጅንስ ሱሪ እና ሹራብ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን በአካል ከጎበኘ በኋላ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ከተማዋን የሚመጥኑ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመገንባት አመራሩ ዓቅሙን አሟጥጦ መሥራት አለበት ብሏል።
ከተማዋ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከመሆኗ አኳያ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የተጠናከረ ፕሮሞሽንም መሠራት እንዳለበት አመልክቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ሰሞኑን የመስክ ምልከታ በተደረገባቸው የባሕር-ዳር እና ኮምቦልቻ እንዲሁም በደብረ-ብርሃን የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ ኃላፊዎች የመሠረተ-ልማት ችግር በስፋት እየተነሳ ስለሆነ የፓርኮቹ አመራሮች ከክልሉ ጋር በቀጥታ በመገናኘት፣ ልዩ ትኩረት እና ክትትል ተደርጎላቸው፣ ችግሮቻቸው በፍጥነት መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የደብረ-ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አጠቃላይ ችግሮቹ እንዲፈቱ ከተማ አስተዳደሩ ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበው ኢንዱስትሪ ፓርኮች መንግሥት ባፈሰሰው የመዋዕለ-ንዋይ ልክ እየለሙ ስላልሆነ ቅድሚያ መሟላት ላለባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በኢንዱስትሪው አካባቢ የደረቅ ወደብ ጉዳይ፣ የፈጣን መንገድ እና ተጨማሪ የኃይል መቀበያ ንዑስ ጣቢያ ጉዳዮች በፌዴራል ደረጃ እንዲፈቱ ለሚመለከተው የፌዴራል መሥሪያ ቤት በማሳወቅ ግፊት ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው መዘጋጀቱንም አክለው ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ አስኪያጅ የሺጥላ ሙሉጌታ የኢንዱስትሪው ሼዶች ሁሉም ሥራ ላይ መሆናቸውን አስረድተው ሌላ ለኢንቨስትመንት የሚሆን 24 ሄክታር መሬት ቢዘጋጅም የመንገድ እና የመብራት ዕጦት ዕንቅፋት መፍጠሩን መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡
የለማ መሬት ኢንዱስትሪው ውስጥ ስላለ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲመጡ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከተው አካል ሆኖ ሊያግዘን ይገባል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ተገልጋዮች መረጃቸውን አሟልተው ከመጡ በበይነ-መረብ ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡